መዝሙር 6 (NASV)
መዝሙር 6
ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር በሸሚኒት6 ርእሱ በሙዚቃ ውስጥ የሚጠቀሙበት ቃል ሳይሆን አይቀርም።።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ በቍጣህ አትገሥጸኝ፤
በመዓትህም አትቅጣኝ።
2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐቅመ ቢስ ነኝና ማረኝ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ ዐጥንቶቼ ተናግተዋልና ፈውሰኝ።
3ነፍሴ እጅግ ታውካለች፤
እስከ መቼ፣ አንተ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ እስከ መቼ ድረስ ይሆናል?
4 እግዚአብሔር ሆይ፤ ተመለስና ሕይወቴን ታደጋት፤
ስለ ጽኑ ፍቅርህም አድነኝ፤
5በሞት የሚያስታውስህ የለምና፤
በሲኦልስ6፥5 ወይም በመቃብር ማን ያመሰግንሃል?
6ከመቃተቴ የተነሣ ዝያለሁ።
ሌሊቱን ሁሉ በልቅሶ ዐልጋዬን አርሳለሁ፤
መኝታዬንም በእንባዬ አሾቃለሁ።
7ዐይኖቼ በሐዘን ብዛት ደክመዋል፤
ከጠላቶቼም ሁሉ የተነሣ ማየት ተስኗቸዋል።
8እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ፤ ከእኔ ራቁ፤
እግዚአብሔር የልቅሶዬን ድምፅ ሰምቷልና።
9 እግዚአብሔር ልመናዬን ሰምቷል፤
እግዚአብሔር ጸሎቴን ይቀበላል።
10ጠላቶቼ ሁሉ ያፍራሉ፤ እጅግም ይደነግጣሉ፤
በመጡበት ይመለሳሉ፤ ድንገትም ይዋረዳሉ።