ኤፌሶን 6 (NASV)
ወላጆችና ልጆች
1ልጆች ሆይ፤ በጌታ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። 2“አባትህንና እናትህን አክብር” በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ 3“መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም”6፥3 ዘዳ 5፥16 የሚል ነው።
4አባቶች ሆይ፤6፥4 ወላጆች ሆይ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።
5ባሮች ሆይ፤ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ፣ በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑት በአክብሮትና በፍርሀት፣ በቅን ልብም ታዘዙ፤ 6ለታይታና ከእነርሱ ሙገሳን ለማግኘት ሳይሆን፣ እንደ ክርስቶስ ባሮች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ በመፈጸም ታዘዟቸው። 7ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ ሆናችሁ በሙሉ ልብ አገልግሉ፤ 8ምክንያቱም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ።
9እናንተም ጌቶች ሆይ፤ ለባሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የእነርሱም፣ የእናንተም ጌታ የሆነው በሰማይ እንዳለ፣ የሰውንም ፊት አይቶ እንደማያደላ ታውቃላችሁና አታስፈራሯቸው።
የእግዚአብሔር ጦር ዕቃ
10በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ። 11የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ። 12ምክንያቱም ተጋድሏችን ከሥጋና ከደም ጋራ ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋራ ነው። 13ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና። 14እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣ 15በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ። 16ከእነዚህም ሁሉ ጋራ፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ 17የመዳንን ራስ ቍር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
18በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ። 19የወንጌልን ምስጢር ለመግለጥ አፌን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በድፍረት እንድናገር ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ጸልዩልኝ። 20በሰንሰለት የታሰረ መልእክተኛ የሆንሁት ለዚሁ ነውና። ስለዚህ መናገር የሚገባኝን ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ።
የመጨረሻ ሰላምታ
21በምን ሁኔታ እንዳለሁና ምን እንደማደርግ ታውቁ ዘንድ ተወዳጅ ወንድምና በጌታ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ቲኪቆስ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል። 22የእኛን ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያበረታ ለዚሁ ስል ወደ እናንተ እልከዋለሁ።
23ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም፣ ፍቅርም ከእምነት ጋራ ለወንድሞች6፥23 ወንድሞች የሚለው የግሪኩ ቃል ወንዶችን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አካል በመሆናቸው ያመኑትን ወንዶችንና ሴቶችንም ያመለክታል። ይሁን።
24ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።6፥24 ጸጋና ዘላለማዊነት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወድዱ ሁሉ ይሁን።