ዘዳግም 29 (NASV)

የቃል ኪዳኑ መታደስ
1 እግዚአብሔር በኮሬብ ከገባው ቃል ኪዳን በተጨማሪ በሞዓብ ምድር ከእስራኤላውያን ጋራ እንዲያደርግ ሙሴን ያዘዘው የኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው።
2ሙሴ እስራኤላውያንን ሁሉ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦
እግዚአብሔር በግብጽ፣ በፈርዖን፣ በሹማምቱ ሁሉና በመላ አገሩ ላይ ያደረገውን ሁሉ ዐይኖቻችሁ አይተዋል። 3እነዚያን ከባድ ፈተናዎች፣ ታምራዊ ምልክቶችና ታላላቅ ድንቆች በገዛ ዐይኖቻችሁ አይታችኋል። 4ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር የሚያስተውል አእምሮ ወይም የሚያይ ዐይን ወይም የሚሰማ ጆሮ አልሰጣችሁም። 5በምድረ በዳ በመራኋችሁ በእነዚያ አርባ ዓመታት ውስጥ ልብሳችሁ አላረጀም፤ የእግራችሁም ጫማ አላለቀም። 6ቂጣ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣችሁም፤ ይህን ያደረግሁት እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ ነው።
7ወደዚህ ስፍራ በደረሳችሁ ጊዜ፣ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎንና የባሳን ንጉሥ ዐግ ሊወጉን መጡ፤ ሆኖም ድል አደረግናቸው። 8ምድራቸውንም ወስደን ለሮቤላውያን፣ ለጋዳውያንና ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠን።
9እንግዲህ የምታደርጉት ሁሉ እንዲከናወንላችሁ፣ የዚህን ኪዳን ቃሎች በጥንቃቄ ተከተሉ። 10እናንተ ሁላችሁ መሪዎቻችሁና አለቆቻችሁ፣ ሽማግሌዎቻችሁና ሹሞቻችሁ እንዲሁም ሌሎች የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል፤ 11ልጆቻችሁና ሚስቶቻችሁ ዕንጨትህን እየፈለጡ፣ ውሃህንም እየቀዱ በሰፈርህ የሚኖሩ መጻተኞችም ዐብረውህ ቆመዋል። 12እዚህ የቆምኸው እግዚአብሔር ዛሬ ከአንተ ጋራ ወደሚያደርገውና በመሐላ ወደሚያጸናው ኪዳን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ጋራ ትገባ ዘንድ፣ 13ለአንተ በሰጠው ተስፋና ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ በማለላቸው መሠረት እርሱ አምላክህ ይሆን ዘንድ፣ አንተም ሕዝቡ መሆንህን በዛሬው ዕለት ለማረጋገጥ ነው። 14እኔም ይህን የመሐላ ኪዳን የማደርገው ከእናንተ ጋራ ብቻ አይደለም፤ 15ዐብራችሁን በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት እዚህ ከቆማችሁት ጋራ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ እዚህ ከሌሉትም ጋራ ነው።
16በግብጽ ምድር እንዴት እንደ ኖርንና ወደዚህ ስንመጣም በየአገሮቹ ውስጥ እንዴት እንዳለፍን ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 17በመካከላቸውም አስጸያፊ ምስሎቻቸውንና የዕንጨትና የድንጋይ፣ የብርና የወርቅ ጣዖቶቻቸውን አይታችኋል። 18የእነዚህን ሕዝቦች አማልክት ለማምለክ ልቡን ከአምላካችን ከእግዚአብሔር የሚመልስ ወንድም ሆነ ሴት ጐሣም ሆነ ነገድ ዛሬ ከመካከላችሁ አለመገኘቱን አረጋግጡ፤ ከመካከልህ እንዲህ ያለውን መራራ መርዝ የሚያወጣ ሥር እንዳይኖር ተጠንቀቁ።
19እንዲህ ያለው ሰው የዚህን መሐላ ቃል በሚሰማበት ጊዜ፣ በልቡ ራሱን በመባረክ፣ “እንደ ልቤ ሐሳብ ብኖርም እንኳ ሰላም አለኝ” ብሎ ያስባል። ይህም በለምለሙም ሆነ በደረቁ መሬት ላይ ጥፋትን ያመጣል29፥19 ወይም፣ ለመርካት ስካርን ይጨምራል።20እግዚአብሔር ለዚያ ሰው ፈጽሞ ይቅርታ አያደርግለትም፤ ቍጣውና ቅናቱ በርሱ ላይ ይነድድበታል። በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ ይወርድበታል፤ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል። 21በዚህ የሕግ መጽሐፍ በተጻፈው የኪዳኑ ርግማን መሠረት፣ እግዚአብሔር እርሱን ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል።
22የሚቀጥለው ትውልድ ከእናንተ በኋላ የሚተኩት ልጆቻችሁና ከሩቅ አገር የሚመጡ እንግዶች በምድሪቱ የደረሰውን ታላቅ መቅሠፍትና እግዚአብሔር ያመጣባቸውን በሽታዎች ያያሉ። 23ምድሪቱ በሙሉ የተቃጠለ ጨውና ዲን ዐመድ ትሆናለች። አንዳች ነገር አይተከልባትም፤ ምንም ነገር አያቈጠቍጥባትም፤ የሚያድግ ተክል አይገኝባትም። የሚደርስባት ውድመት እግዚአብሔር በታላቅ ቍጣ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፣ እንደ አዳማና ስቦይ ጥፋት ይሆናል። 24አሕዛብም ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በዚህች ምድር ላይ ይህን ለምን አደረገባት? ይህ አስፈሪና የሚነድድ ቍጣስ ለምን መጣባት?” ብለው ይጠይቃሉ።
25መልሱም፣ “የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር ባወጣቸው ጊዜ፣ ከእነርሱ ጋራ የገባውን ኪዳን ሕዝቡ ስለ ተዉ ነው። 26ወጥተውም የማያውቋቸውን፣ እርሱም ያላዘዛቸውን ሌሎችን አማልክት አመለኩ፤ ሰገዱላቸውም። 27ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ርግማን ሁሉ እስኪያመጣባት ድረስ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በዚህች ምድር ላይ ነደደ። 28በአስፈሪ ቍጣና በታላቅ መዓት እግዚአብሔር ከምድራቸው ነቀላቸው፤ አሁን እንደ ሆነውም ወደ ሌላ ምድር ጣላቸው” የሚል ይሆናል።
29ምስጢር የሆነው ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ እንከተል ዘንድ ለዘላለም የእኛና የልጆቻችን ነው።