2 ዜና መዋዕል 13 (NASV)

የይሁዳ ንጉሥ አብያ
13፥1-2፤ 13፥22–14፥1 ተጓ ምብ – 1ነገ 15፥1-2፤ 15፥6-8
1ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ አብያ በይሁዳ ነገሠ። 2በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ዓመት ገዛ። እናቱ ሚካያ13፥2 ብዙ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች የሱርስቱ ቅጅ (እንዲሁም 2ዜና 11፥20 እና 1ነገ 15፥2) ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ ግን፣ ሚካያ ይላል። ትባላለች፤ እርሷም የጊብዓ ተወላጅ የኡርኤል ልጅ ነበረች።
በአብያና በኢዮርብዓምም መካከል ጦርነት ነበር። 3አብያ አራት መቶ ሺሕ ብርቱ ተዋጊዎች ይዞ ዘመተ፤ ኢዮርብዓምም ስምንት መቶ ሺሕ ብርቱ ተዋጊዎች ይዞ በመውጣት ጠበቀው።
4አብያ በኰረብታማው በኤፍሬም አገር በጽማራይም ተራራ ላይ ቆሞ፣ እንዲህ አለ፤ “ኢዮርብዓምና እስራኤል ሁሉ ስሙኝ! 5የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ዳዊትና ዘሮቹ በእስራኤል ላይ ለዘላለም እንዲነግሡ በጨው ኪዳን የሰጣቸው መሆኑን አታውቁምን? 6የዳዊት ልጅ የሰሎሞን ባሪያ የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ግን በጌታው ላይ ዐመፀ። 7የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም ገና ሕፃን ሳለ፣ ምንም ማድረግ በማይችልበትና እነርሱንም ለመቋቋም ዐቅሙ በማይፈቅድለት ጊዜ የማይረቡ ምናምንቴዎች በዙሪያው ተሰበሰቡበት፣ በረቱበትም።
8“አሁንም እናንተ በዳዊት ዘርዐ ትውልድ እጅ ያለውን የእግዚአብሔርን መንግሥት ልትቋቋሙ ዐስባችኋል። በርግጥም በሰራዊት ረገድ እጅግ ብዙ ናችሁ፤ አማልክታችሁ ይሆኑ ዘንድ ኢዮርብዓም የሠራቸውንም የወርቅ ጥጆች ይዛችኋል። 9ደግሞስ የአሮን ልጆች የሆኑትን የእግዚአብሔርን ካህናትና ሌዋውያንን አባርራችሁ፣ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ እናንተም የራሳችሁን ካህናት አልሾማችሁምን? አንድ ኰርማና ሰባት አውራ በግ ይዞ ራሱን ለመቀደስ የሚመጣ ማንኛውም ሰው አማልክት ላልሆኑ ለእነዚያ ጣዖታት ካህን ይሆናል።
10“ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱንም አልተውንም፤ እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ ያሉት ካህናት የአሮን ልጆች ሲሆኑ፣ ረዳቶቻቸውም ሌዋውያኑ ናቸው። 11እነርሱም በየጧቱና በየማታው የሚቃጠል መሥዋዕትና ሽታው ደስ የሚያሰኝ ዕጣን ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፤ የገጹን ኅብስት በሥርዐቱ መሠረት በነጻው ጠረጴዛ ላይ ያኖራሉ፤ በየማታውም በወርቁ መቅረዝ ላይ ያሉትን ቀንዲሎች ያበራሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እናንተ ግን ትታችሁታል። 12እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው፤ መሪያችንም እርሱ ነው። መለከት የያዙ ካህናቱም የጦርነቱን ድምፅ በእናንተ ላይ ያሰማሉ። እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ አይቀናችሁምና፣ ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋራ አትዋጉ።”
13በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከሰራዊቱ ከፊሉን ከይሁዳ ሰራዊት በስተጀርባ እንዲያደፍጡ ላከ፤ የቀረውም ሰራዊት ከርሱ ጋራ የይሁዳን ሰራዊት ፊት ለፊት እንዲገጥሙ አደረገ። 14የይሁዳም ሰዎች ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከፊትና ከኋላ መከበባቸውን አዩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፤ ካህናቱም መለከታቸውን ነፉ። 15የይሁዳም ሰዎች በፉከራ የጦርነት ድምፅ አሰሙ፤ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት ፈጽሞ መታቸው። 16እስራኤላውያን ከይሁዳ ፊት ሸሹ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 17አብያና ሰዎቹም ከባድ ጕዳት አደረሱባቸው፤ ከዚህ የተነሣም ከእስራኤል ብርቱ ተዋጊዎች መካከል ዐምስት መቶ ሺሕ ሰዎች ተገደሉ። 18በጦርነቱም የእስራኤል ሰዎች ተዋረዱ፣ የይሁዳ ሰዎች ግን በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነዋልና ድል ነሡ።
19አብያም ኢዮርብዓምን አሳድዶ የቤቴልን፣ የይሻናንና የዔፍሮንን ከተሞች ከነመንደሮቻቸው ወሰደበት። 20ኢዮርብዓም በአብያ ዘመን እንደ ገና ሊያንሰራራ አልቻለም፤ ከዚያም እግዚአብሔር ስለ ቀሠፈው ሞተ።
21አብያ ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ ዐሥራ አራት ሚስቶች አግብቶም ሃያ ሁለት ወንዶችና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆች ነበሩት።
22በአብያ ዘመን የተከናወነው ተግባር፣ እርሱ የፈጸመውና የተናገረው ሁሉ በነቢዩ በአዶ የታሪክ መዛግብት ተጽፏል።